የእነ ጉርሜሳ አያናን መዝገብ የሚያየው 4ኛ ችሎት መዝገቡን ለዛሬ ሰኔ 9/2009 የቀጠረው ብይኑን ለማሰማት የመጨረሻ ቀጠሮ በማለት ቢሆንም ብይኑ ዛሬም እንዳላለቀላቸው ተናግረዋል። የ19 ተከሳሾችን ሰርተው እንደጨረሱ እና የቀራቸው የ3ት ተከሳሾች ብቻ መሆኑን የተናገሩት ዳኞቹ ” በባለፈው ቀጠሮ እናንተም አትጨርሱም ብላችሁን ነበር። የናንተን ምክር ብንሰማ ጥሩ ነበር። ጥቂት ቀን ይበቃናል።” በማለት ለሰኔ 15/2009 ቀጠሮ ሰጥተው የማይመቸው ጠበቃ ካለ በቢሮ እንዲያናግሯቸው ገልፀው የእለቱ ችሎት ተጠናቋል። ጠበቆች ዳኞቹን በቢሮ በኩል በማናገር ቀጠሮው ለሰኔ 16/2009 ቀን ከሰአት እንዲሆን ተስማምተዋል።
በእነ ጉርሜሳ አያና መዝገብ የተከሰሱ 22 ተከሳሾች ለ4ት ወር ያክል ማእከላዊ ከቆዩ በኋላ፤ ሚያዚያ 14/2008 ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን የካቲት 22/2009 ቀን የአቃቤ ህግ ማስረጃዎች ተሰምቶ ካበቃ በኋላ ለብይን ሲቀጠር 3ት ወራት አልፏል። አቃቤ ህግ በማስረጃነት ያሰማቸው ከ5ኛ እና 11ኛ ተከሳሾች ከላፕቶፕ ላይ ተገኝተዋል የተባሉ ኦሮምኛ ዘፈኖች እና 4ኛ ተከሳሽ (በቀለ ገርባ) ኦሳ (OSA) ላይ በእንግሊዘኛ ያደረገው ንግግር በፍርድ ቤቱ የስራ ቋንቋ (አማርኛ) አልተተረጎመም እየተባለ ተደጋጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮዎች ሲሰጥ ነበር። የትረጉም ስራው ተጠናቆ ለፍርድ ቤቱ ከደረሰ በኋላም ዳኞች ብይኑ እንዳልጨረሱ እየተናገሩ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠታቸውን ቀጥለዋል።
ከየካቲት 22/2009 ቀን (ለመጀመሪያ ጊዜ ለብይን የተቀጥበት ቀን) ጀምሮ የነበረውን የችሎት ሂደት ከዚህ በታች ባለው ሰንጠረዥ ማየት ይቻላል።
Advertisements